የአዳማ ከተማ እግር ኳስ ክለብ አመራር አካላት የክለቡ ቦርድ አመራር፤የከተማው ካቢኔ እና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በአንድ አመት ብሄራዊ ሊግ ቆይታ ወደ ነበረበት ፕሪሚየር ሊግ ለማሳደግ ከመጀመሪያው ከ2005 ዓ.ም ከወረደበት ጊዜ አንስቶ መሰረታዊ የክለቡን ነባራዊ ችግሮች ላይ ጥናት በማድረግ የክለቡን አደረጃጀት በተወሰነ ደረጃ በማስተካከል እና ልምድ ያላቸውን አሰልጣኞች፤ስፖርተኞችን በመመልመል፤ለክለቡ የሚያስፈልገውን አቅርቦት በማሟላት እና ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ ውጤታማ ስራዎችን አከናውኗል፡፡በዚህም መሰረት ክለቡ በቂ ቅድመ ዝግጅት አካል ብቃት እና መሰረታዊ ስልጠና በመስጠት ከተለያዩ ክለቦች ጋር የአቋም መለኪያ ውድድሮችን በማድረግ ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ ወደ ውድድር ገብቷል፡፡

በ2006 ዓ.ም.ሀገር አቀፍ የብሄራዊ ሊግ እግር ኳስ ውድድር በሀገሪቱ ከተለያዩ ክልሎች የሚገኙ 69 ክለቦች መካከል በ 7 የምድብ ዞኖች ተከፍሎ የተደረገ ወድድር ሲሆን ከነዚህም ምድቦች አንደኛ እና ሁለተኛ በሚወጡ የመጨረሻዎቹ 16 ክለቦች መካከል በሚደረግ ውድድር 1ኛ እና 2ኛ የሚወጣ ክለብ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የማለፍ የውድድር መርሃ ግብር እንደመሆኑ ውድድሩ አድካሚ፣ጥንቃቄ እና መስዋትነትን የሚጠይቅ ውድድር እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በዚህም የውድድር መርሃ ግብር ክለባችን ካለበት የምስራቅ ዞን ምድብ 10 ክለቦች ውስጥ የምድቡ ጨዋታ ሳይጠናቀቅ አንደኛነቱና በማረጋገጥ በመጨረሻው በባህዳር ከተማ የ 16ቱ ክለቦች ላይ 1ኛ በመውጣት እና የሊጉ ሻምፒዮና በመሆን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ መቀላቀል ችሏል ፡፡
በአጠቃለይ ክለባችን በ2006 ዓም በተደረጉ የብሄራዊ ሊግ ውድድሮች ያስመዘገባቸው ውጤት
 የመጀመሪያው የምድቡ የደርሶ መልስ ባደረጋቸው ውድድር ያስመዘገበው ውጤት፡-በአጠቃላይ ከምድቡ ከተወዳደራቸው 18 ውድድሮች ውስጥ 13 ወድድር በማሸነፍ፤2 በመሸነፍ፤3 ጊዜ አቻ በመውጣት፤36 ግቦችን በማስቆጠር፤9 ግብ ተቆጥሮበት በአጠቃላይ 39 ነጥብ በማስመዝገብ አንድ ጨዋታ እየቀረው አንደኛነቱን አረጋግጦ ወደ 16ቱ ክለቦች የመጨረሻ ውድድር ማለፍ ችሏል፡፡
 የመጨረሻው የ 16 ክለቦች የባህር ዳር ከተማ በተደረገ ውድድር ክለባችን ስድስት ጨዋታዎችን በመወዳደር አምስቱን ግጥሚዎች በማሸነፍ፤አንድ አቻ በመውጣት፤አስራ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር፤ስድስት ግቦች ተቆጥረውበት አጠቃላይ የብሄራዊ ሊጉ ውድድር አንደኛ በመውጣት ሻምፒዮና መሆን ችሏል፡፡
 በዚህም አጠቃላይ ውጤት ዋንጫ ያስመዝገብንበትን ስናይ፤በባህር ዳር ውድድሩ በየውድድሩ 4 ምርጥ ስፖርተኞችን በማስመረጥ 4 ዋንጫ፤ምርጥ ክለብ በመሆን 1 ዋንጫ፤በዙሩ አንደኛ በመሆን 1 ዋንጫ፤አጠቃላይ የሊጉ ሻምፒዮና በመሆን 1 ዋንጫ፤ኮከብ አሰልጣኝ በማስመረጥ 1 ዋንጫ፤በአጠቃላይ 8 ዋንጫዎችን በማግኘት አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ የመጨረሻውን ወደ ፕሪሚየር ሊግ የመመለሱን ግባችንን አሳክተናል፡፡
በዚህም መሰረት ክለባችን ይሄንን አመርቂ ውጤት ያስመዘገበበት ምክንያት የክለቡ አመራር አካላት ቦርድ፤የከተማው ካቢኔ አባላት፡የክለቡ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ቀጣይነት ያለው ያላሰለሰ ድጋፍ እና ክትትል በማድረጋቸው፤አሰልጣኞች፤ስፖርተኞች ባደረጉት ተነሳሽነት፤ቁርጠኝነት፤ቡድናዊ ጥምረት እና ያላሰለሰ ጥረት እንዲሁም የአዳማ ክለብ ደጋፊዎች ክለቡን በማበረታት በተሰራው ቅንጅታዊ ስራ ነው፡፡
ክለባችን በአመቱ የብሄራዊ ሊጉ ሻምፒዮና በመሆን ወደ አዳማ ከተማ በገባበት እለት የአዳማ ከተማ አስተዳድር እና የክለቡ ደጋፊ ማህበረሰብ ከፍተኛ አቀባበል በማድረግ የከተማው ባለኃብቶችም ለክለቡ አባላት የእራት ግብዣ በማድረግ የክለቡን አባላት በማበረታት በደፊትም ከክለቡ ጎን እንደሚቆሙ እረጋግጠዋል፡፡
በተጨማሪም የከተማው መስተዳድር ክለቡ ውጤት በማስመዝገብ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በመመለሱ በገባው ቃል መሰረት ለክለቡ አባላት እና ተጨዋቾች የ 3 ሚሊየን ብር ሽልማት አበርክቷል፡፡ይህም የክለቡን አባላት ለከፍተኛ ኃላፊነት እና በክለቡ ከፍተኛ አመኔታ እንዲኖራቸው የሚያደርግ በመሆኑ ለሌሎችም ክለቦች አርአያ ሊሆን የሚገባው ተግባር አከናውኗል፡፡